(ጥቅምት 04 ቀን 2017 ዓ.ም. ሞስኮ):- 17ኛው የሰንደቅ ዓላማ ቀን የኤምባሲው ባልደረቦች በተገኙበት ”ሰንደቅ ዓላማችን ለብሔራዊ አንድነታችን፣ ለሉዓላዊነታችንና ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል በኤምባሲው ተከብሯል።
የእለቱ ስነ-ስርዓቱ በኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር የተጀመረ ሲሆን ቀኑን አስመልክቶ የሚሲዮኑ መሪ ክቡር አምባሳደር ገነት ተሾመ(ዶ/ር) መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ክቡር አምባሳደር እንኳን ለ17ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን አደረሳችሁ መልዕክት በማስተላለፍ ሰንደቅ ዓላማችን የኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን የጋራ ዓርማ በመሆኑ እለቱን ስናከብር ሰንደቅ ዓላማችን የነፃነታችን ምልክት፣ የድላችን ዓርማ፣ የሉዓላዊነታችን መገለጫ እንዲሁም የኅብረ ብሔራዊ አብሮነታችን ዋስትና እንደሆነ በመረዳት ተገቢውን ክብርና ፍቅር መስጠት እንደሚገባ ጠቁመው የአገራችንን ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት ከኢትዮጵያ አልፎ ሌሎች በርካታ አገራት እንደነጻነት በመቁጠር እየተጠቀሙበት እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ ዓለም ዓቀፍ መድረኮች ላይ አገራችንን የሚወክሉ ተቋማና ግለሰቦች እንዲሁም አትሌቶቻችን በተሳተፉበት ውድድር ላይ ሲያሸንፉ ሰንደቅ ዓላማችን ሲውለበለብ ልዩ ስሜት ስለሚፈጥር ዜጎች በሰንደቅ ዓላማ ፊት ቆመው ቃለ-መሃላ በመፈጸም ለአገራቸውና ለሰንደቅ ዓላማቸው ያላቸውን ክብርና ፍቅር ዳግም የሚገልጹበትና የአገራቸውን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ቃላቸውን የሚያድሱበት ትልቅ ዕሴት በመሆኑን ገልፀዋል።
በመጨረሻም የኤምባሲው ባልደረቦች የ17ኛው ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን በዓል ቃለ መሃላ ፈጽመው የእለቱ ፕሮግራም ተጠናቋል፡፡